የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን የተቋቋሙበትን የኢትዮጵያ ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው – ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን የተቋቋሙበትን የኢትዮጵያ ሕግ የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
“የሃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ለሰላምና አብሮነት” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት የሃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን የይዘት ሥራዎችን በመከታተልና በመገምገም የእርምት እርምጃ ይወስዳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን አብዛኞቹ በመርሕ ላይ የተመሰረቱ ሃይማኖታዊ ይዘቶችን ይሰራሉ።
ይሁን እንጂ ከሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን መካከል ጥቂት እኩይ ዓላማ ያላቸው የሌሎችን በጎ ስራ እያበላሹ ነው ብለዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የተመዘገቡት በኢትዮጵያ ሕግ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
የእምነት ተቋማት ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። ነገር ግን ነገር ግን ሀገር ድንበርና ሉዓላዊነት ስላላት ያንን ማክበር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የተነሣ በኢትዮጵያ ውስጥ እና ውጭ ያሉ ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ሰዎች የሚጠየቁት በራሳቸው ሀገር ሕግ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን እንዲቋቋሙ የተጠየቀው ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ለማስረፅ ይፈቀድልን በሚል መሆኑን ገልጸው፤ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ መስራት ሕግ መተላላፍ ነው ብለዋል።
ስለሆነም የሚሻሻል ሕግ አለ ከተባለ ይሻሻልልን ብለው መጠየቅ እንጂ ከሕግ ውጭ መንቀሳቀስ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የሃይማኖት ሚዲያዎች ለጋራ ሕዝብና እሴት መጎልበት ያላቸውን ገንቢ ሚና ሲወጡ ሌሎች ጥያቄዎቻቸው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የጋራ ኅብረት በመፍጠር ራሳቸውን በራሳቸው ማረምና የተደራጀ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸው፤ መንግሥት ለኅብረቱ መመስረት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እንደሀገር ለመቀጠሏ የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በተደነገገው መሰረት ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ገልጸው፤ ነፃነትን ለማፅናት በኃላፊነት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን መኖራቸው ፀጋ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለሕዝብ አብሮነትና ሰላም ግንባታ ድርሻው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የአብሮነት ፀጋዎች የመሆናቸውን ያህል ስህተታቸው ለዘመናት የኖረን የአብሮነት ገመድ ይበጥሳል ብለዋል።
በመሆኑም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ሀላፊነት ስላለባቸው፣ ከአውድ ሲወጡ መንግሥት ሕግ እንደሚያስከብር ገልጸዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት፤ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ከሃይማኖት ባሻገር የህብረተሰቡን ማህበራዊ እሴቶች ማንጸባረቅ አለባቸው።
ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ ሰላም፣ ደህንነትና ሕልውና ላይ ልዩነት ሊኖራቸው እንደማይገባ ገልጸዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምና መቻቻልን እንደሚሰብኩ ገልጸው፤ ከማህበረሰቡ እሴት ግንባታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ መስራት አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።