የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 20 ሚሊየን ብር መደበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 20 ሚሊየን ብር መደበ።
የማህበሩ ዋና ፀሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ፥ ማህበሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚውል 20 ሚሊየን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከእህት ማህበራት ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም 5 ሺህ የፊት መሸፈኛ ማስኮች፣ 6 ሺህ የሰርጅካል ጓንቶችን፣ 1 ሺህ 500 የህክምና ጫማዎች፣ 1 ሺህ የፕላስቲክ የፊት መከላከያ እና 5 ሺህ የመለያ ገዋኖችን ለመግዛት መታቀዱንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ500 በላይ አምቡላንሶች አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ዝግጁ ሆነዋልም ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በፌደራል እና በክልል ያሉት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በማስተባበር እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የማህበሩ በጎ ፈቃደኞች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በአውሮፕላን ማረፊያ፣ ከአጎራባች ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ኬላዎች ለሚገቡ ሰዎች የሙቀት ልየታ እየሰሩ መሆናቸውን አውስተዋል።
ማህበሩ ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።