በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበው የዲጂታል ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጂታል ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሯ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ100 ቀናት ግምገማ እና የበጀት ዓመቱ የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም ዲጂታል ኢትዮጵያን እንደ ኢኒሼቲቭ በመያዝ በርካታ ሥራዎች መሰራቱን ገልጸው÷ ከእነዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም አገልግሎትን በጥራት እና በፍጥነት እንዲዳረስ በማድረግ ብልሹ አሰራር እንዲቀረፍና የተገልጋዮችን እንግልት፣ የሚያጠፉትን ጊዜ እና ወጪን እንዲቀንስ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌላኛው የፋይዳ መታወቂያ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ይህም አገልግሎትን ለዜጎች በፍትሃዊነት ለማድረስ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።
የሕግ ተገዢነትን ከማረጋገጥ አኳያም ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው በመግለጽ÷ አሁን ላይ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕብረተሰብ ጋር እንዲደርስ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ዘርፍም የሰው ሃብት ልማትን በማሳደግ ረገድ የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንስተው÷ በዚህም በርካታ የስልጠና ማዕከላት በተለያዩ ተቋሞቻችን እየተሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የኦንላይን አገልግሎቶች መጨመራቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ÷ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች የተለመደውን የባንክ ለባንክ ክፍያን በብዙ ዕጥፍ መብለጥ እንደቻለም አብራርተዋል።
በዮናስ ጌትነት