Fana: At a Speed of Life!

ኔቶ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱን አምኗል – ሜድቬዴቭ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱን የኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልተንበርግ በተዘዋዋሪ ማመናቸውን የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ገለጹ፡፡

ማክሰኞ ዕለት በጉዳዩ ላይ ስቶልተንበርግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ “ሩሲያ በጦርነቱ ባለድል ከሆነች ለኔቶ ሽንፈት ይሆናል” ማለታቸው ይታወሳል።

የኖርዌዩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዬንስ ስቶልተንበርግ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሠጡት በዛሬው ዕለት የኔቶ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች ከዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር አሌክሲ ሬዝኒኮቭ ጋር ለመገናኘት በተዘጋጁበት ወቅት ላይ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ሜድቬዴቭ “ቀናው ኖርዌያዊው የኔቶ ባልደረባ በመጨረሻ እውነቱን አምነዋል” ብለዋል።

ሚኒስትሮቹ በዛሬው ስብሰባ ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ የሩሲያን ጦር ዩክሬንን በመርዳት ማሸነፍ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል፡፡

የኔቶ አባል ሀገራት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊ ዕርዳታ ወደ ዩክሬን እንደላኩ መገለጹ ይታወቃል።

ከዚህ በኋላ የዩክሬንን “አስቸኳይ የወታደራዊ አቅርቦት ፍላጎቶች” በቀጣይ እንዴት ማሟላት እንደሚችሉ እና የራሳቸውን የጦር መሣሪያ ክምችት እንዴት እንደሚያሳድጉ ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ስቶልተንበርግ ዩክሬን በጠየቀችው መሰረት ከአባል ሀገራቱ የአየር ኃይል ፣ የሚሳኤል እንዲሁም የሌሎች ዘመናዊ መሣሪያዎች ድጋፍ በአስቸኳይ ይቀርብላታል ነው ያሉት።

የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬን ጦርነቱን ማሸነፍ አለባት በሚለው ሃሳብ እንደሚያምኑ እና ይህንንም ለማረጋገጥ የሞራል፣ የፖለቲካ እና የደኅንነት ድጋፍ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.