ሩሲያ ከሀገራት እንዳይገቡ የጣለችውን የገቢ የምግብ ምርቶች እገዳ አራዘመች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀደም ሲል ሀገራቸው ላይ ማዕቀብ ከጣሉ ሀገራት የምግብ ምርቶች ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ ያሳለፉትን ክልከላ አራዘሙ።
በፈረንጆቹ 2014 ክሬሚያ ሩሲያን ከተቀላቀለች በኋላ ምዕራባውያኑ እውቅና አንሰጥም ማለታቸው እና ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ሩሲያ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 2014 ጀምሮ ከምዕራባውያኑን አንዳንድ የምግብ ምርቶች እንዳይገቡ በማገድ አፀፋዊ ምላሽ ሰጥታለች።
አሁን የተራዘመው እገዳ እስከ ፈረንጆቹ ታኅሣሥ 31 ቀን 2023 እንደሚቆይም ነው የተነገረው፡፡
ሩሲያ በገቢ የምግብ ምርቶች ላይ የወሰደችው የእግድ እርምጃ በዓመታት ለበርካታ ጊዜ ሲራዘም እና ማስተካከያ ሲደረግለት መቆየቱን አስታውሶ አርቲ ዘግቧል፡፡
እገዳው በመጀመሪያ ተግባራዊ የሆነው ከአሜሪካ ፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኖርዌይ እና ከካናዳ በሚገቡ የተወሰኑ የምግብ ምርቶች ላይ ነበር።
ኋላ ላይም በፈረንጆቹ 2015 አልባኒያ ፣ ሞንቴኔግሮ ፣ አይስላንድ እና ሊሌችተንስታይንን በማካተት እገዳው መጠናከሩ ይታወሳል።
ከአንድ ዓመት በኋላ በ2016 ደግሞ ዩክሬን የእገዳው አካል ሆናለች፡፡
እገዳው የተወሰኑ የምግብ ዓይነቶች እና ጥሬ እቃዎች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡
ስጋ እና የስጋ ተዋፅዖ ፣ ወተት እና የወተት ተዋፅዖዎች ፣ ዓሳ እና የዓሳ ተዋፅዖዎች እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬዎች ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ የተከለከሉ የገቢ ንግድ ምርቶች ናቸው፡፡
ከፈረንጆቹ ጥቅምት 2017 ጀምሮ ደግሞ በአሳማ የስጋ ምርቶች እንዲሁም በእንስሳት ተረፈ ምርቶች ላይ እገዳው ተግባራዊ ሆኗል፡፡
የተከለከሉ ገቢ ምርቶች በሀገሪቷ ከተገኙም እንዲወገዱ የፑቲን አስተዳደር ውሳኔ አሳልፏል፡፡