Fana: At a Speed of Life!

15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ክልሎች ተከበረ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ክልሎች ተከበረ።

በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው በቀርያን ዶዳን አዳራሽ በቀጥታ እየተከበረ ሲሆን በሌሎች የክልሉ ከተሞችም በድምቀት ተከናውኗል።

በተመሳሳይ 15ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በፖናል ውይይት ተከብሯል፡፡

ቀኑ “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሶሶ” በሚል መሪ ቃል ነው በቦንጋ የተከበረው፡፡

እንዲሁም በሲዳማ ክልል 15ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝኃነታችን መገለጫ፣ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ቃል ሰንደቅ ዓላማ መስቀልን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በዝግጅቱ ላይ ከርዕሰ መስተደድር ደስታ ሌዳሞ በተጨማሪ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ሰራተኞች፤ የፀጥታ አካላት እንዲሁም የሀዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ ቀኑ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባኤ ኤሊያስ ኡመታ ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነት መግለጫ መሆኑን ገልጸው ለሰንደቅ አላማ ከምን ጊዜውም በላይ ክብር እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ 15 ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በድሬዳዋ አስተዳደር ተከብሯል ።

ቀኑ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ነው የተከበረው፡፡

እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በዓሉ “ሰንደቅ አላማችን የብዝሀነታችን መገለጫ፣ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሥነሥርዓቶች ተከብሯል።

የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት እና የማንነት መገለጫ በመሆኑ ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እና የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችንን በጋራ በመመከት የአገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።

 

 

 

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.