ተመድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድህነት ቅነሳ ላይ እንዲረባረብ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የድህነት ቅነሳ ላይ እንዲረባረብ ጠየቀ፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥያቄውን ያቀረቡት ትናንት በተከበረው “ዓለም አቀፍ የድህነት ቅነሳ ቀን” ላይ መሆኑን ሺንዋ ዘግቧል፡፡
ዋና ጸሐፊው ÷ “ይህን ቀን እያከበርን ባለበት ወቅት ዓለማችን ከነበረችበት የዕድገት ደረጃ ወደ ኋላ እየተጓዘች መሆኑን ልንክደው የማንችለው መራር እውነት ነው” ብለዋል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፣ የዓየር ንብረት ለውጥ እና ጦርነት ሚሊየኖችን ለድኽነት እና ለከፋ ድኽነት እንዲዳረጉ ምክንያት መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ÷ በዓለም ወቅታዊ ሁኔታ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ይበልጥ መጎዳታቸውንና እየተጎዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻርም እንዲያገግሙ ድጋፍ ማድረግ እና የብድር እፎይታ ጊዜ ማመቻቸት ይገባል ነው ያሉት።
ዘላቂ የልማት ግቦች ተብለው የተቀመጡት ዝርዝር ተግባራትም በወረቀት ደረጃ ብቻ ሰፍረው እንዳይቀሩ ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
“ዓለም አቀፉ የድህነት ቅነሳ ቀን” መርሐ-ግብር ከመቼውም በላይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማንቂያ ደወል ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፥ ሁሉም በጤና፣ ሥራ፣ ሥርዓተ-ፆታ፣ የማኅበረ-ሰብ አገልግሎት፣ የምግብ አቅርቦት እና የትምህርት ሥርዓት ለውጥ ላይ ተደጋግፎ በፍጥነት ሰው ተኮር መፍትሄ ላይ እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡
ታዳጊ ሀገራት ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚና ታዳሽ የኃይል አማራጭ የሚያደርጉትን ሽግግር መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።