የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካን መፃኢ እድል ለመወሰን በውስጣቸው ትልቅ አቅም አለ – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካን መፃኢ እድል ለመወሰን በውስጣቸው ትልቅ አቅም እንዳለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
አቶ ደመቀ መኮንን በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካን መፃኢ እድል ለመወሰን በውስጣቸው ትልቅ አቅም አለ ብለዋል።
”የቀደመ የፓን አፍሪካኒዝም ታሪካችን ወደ አዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ የተጠናከረች አፍሪካን መፍጠር ይገባል” ሲሉም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በአህጉር ደረጃ ያሉ መልካም እድሎችን በመጠቀም ለወጣቶች እድገት እና ተጠቃሚነት መስራት ይገባናል ብለዋል።
መንግስት ለወጣቶች ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል።
የጉባኤው አላማም ይህን ታላቅ አቅም በተሳሰረ አንድነት እንዲያወጡት ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም አፍሪካን የበለፀገች እንዲሁም ከተፅዕኖዎች ሁሉ የፀዳች አድርጎ ለመቅረፅ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ያለመ ነው ማለታቸው የብልጽግና ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ÷ አፍሪካ ያላትን የወጣቶች አቅም በመጠቀም ተስፋ እና ጥንካሬ ማሳደግ ይገባታል ብለዋል።
ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለአህጉሩ ልማት እና እና ሁለተናዊ ለውጥ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት አስፋው ተክሌ÷ በነፃነት ትግል ውስጥ ያደረገውን ጥረት በአሁኑ ዘመን የሚገኙ በልማት ዘርፎችም ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስተዋወቅና አብሮነትን ማጠናከር ዓላማው ባደረገው ጉባዔ ከ50 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት መሪዎች ተሳታፊ ናቸው።