በመዲናዋ የአዲስ ከተማ መለስተኛ መናኸሪያ አገልግሎት ወደሌሎች መናኸሪያዎች እንዲዛወር ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አውቶብስ ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘው መለስተኛ መናኸሪያ አገልግሎት ወደሌሎች መናኸሪያዎች እንዲዛወር መደረጉን የትራንስፖርት ባለሥልጣን አመለከተ።
ባለሥልጣኑ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ በመናኸሪያዎች የሰዎችን ጥግግት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሰዎች ጥግግትን በመቀነስ ማኅበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ እየተሞከረ ይገኛል።
መናኸሪያዎች ከፍተኛ የሕዝብ ምልልስ ያለበትና የተሳፋሪ ጥግግት በብዛት የሚታይበት በመሆኑ ማኅበራዊ ርቀት በማስጠበቅና ንክኪን በመቀነስ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የሰው ጥግግትን ለመቀነስ በአዲስ ከተማ መለስተኛ መናኸሪያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሌሎች መናኸሪያዎች በማዛወር አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህም መሠረት የሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ቱሉቦሎ፣ ወሊሶ፣ ወልቂጤና ሰባት ቤት ጉራጌ ሥምሪቶች በአየር ጤና መናኸሪያ የሚሰጡ ሲሆን የአዳማና ቢሾፍቱ ሥምሪቶች ደግሞ በላምበረት እና በቃሊቲ መናኸሪያዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተዛውረው አገልግሎት የሚሰጡ
ይሆናል።
ባለሥልጣኑ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት አዲስ አበባ ባሉ መናኸሪያዎች መንገደኞች እጃቸውን እንዲታጠቡ፣ የእጅ ማጽጃ ኬሚካሎችን እንዲጠቀሙና ተሽከርካሪዎች በአልኮል እንዲያጸዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች ባለሥልጣኑ እያከናወነ ሲሆን ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ኮሚቴ አቋቁሞ በሁሉም መናኸሪያዎች ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።