ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወታቸው አለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ በጭነት መኪና ውስጥ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ህይወት መለፉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዜጎች ላይ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ፤ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
የሟቾቹን ብዛት እና መሰል ዝርዝር መረጃዎች በቀጣይ እንደሚያሳውቅ የገለጸው ሚኒስቴሩ፥ በጉዳዩ ዙሪያ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በሞዛምቢክ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ቢቢሲ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ደግሞ ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ውስጥ ቢያንስ 64 ኢትዮጵያዊያን በመተፋፈግ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል።