የሰላም ስምምነቱ ከግብ እንዲደርስ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል – ዶ/ር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱ ከግብ እንዲደርስ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑት÷ የጦርነትና ግጭቶች መቋጫው ዘላቂ ሰላምን ያረጋገጠ እንዲሆን ለማድረግ መስዋዕትነትን የሚከፍሉ ሃይሎች ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ ብለዋል፡፡
እነዚህ ጀግኖች በሽግግር ፍትህና በፅኑ መሰረት ላይ በተገነባ ማንነትና ድርጊት ይታነፃሉ ያሉት አቶ ለገሰ÷ የጀግኖች ወሮታ ጠንካራ ሀገርና የሀገረ-መንግስት ግንባታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህን ሃቅ የብዙ ሀገራትን ታሪክ መለስ ብሎ የቃኘ ሰው ሊረዳው ይችላል፤በእኛም ሀገር የተጀመረው የሰላም ጥረት እንዲሳካ ብዙዎች መስዋዕትነትን ከፍለዋል ብለዋል፡፡
የሰላም ጥረቱ ከዳር እንዲደርስ፣ የህዝባችን መሻት እውን እንዲሆን እና ያስቀመጥናቸው ሀገራዊ ግቦች እንዲሳኩ ሁላችንም የሰላም ስምምነቱን መርሆዎች ማክበር ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ከጥላቻ ንግግሮች፣ ብሽሽቆች፣ የከፋፋይነት እሳቤዎችና አብሮነታችንን ከሚበትኑ ድርጊቶች ራስን መቆጠብ፣ ሌላውንም ማረቅ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የተጀመረው የሰላም ጥረት ከግብ እንዲደርስ እና መላው ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡