Fana: At a Speed of Life!

አቶ ርስቱ ከተመድ የሥነ ህዝብ ፈንድ እና ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ከተባበሩት መንግስታት የሥነ ህዝብ ፈንድእና ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ተወካዮች ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም የሴቶችና ህጻናትን ህይወት ማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
 
የተባበሩት መንግስታት የሥነ ህዝብ ፈንድ ኢትዮጵያ ተወካይ ሱዛን ማንዶንግ÷በክልሉ ጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳ፣በገደብ እና በይርጋ ጨፌ ወረዳዎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ጾታዊ ጥቃት መከላከል ላይ እና በሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ላይ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
 
በጌዴኦ ዞን ተዘዋውረው በተመለከቱባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የህዝብ አሰፋፈር ያለበት እንደመሆኑ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
በኢትዮጵያ ከሚካሔደው የሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
 
የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በዘላቂ የልማት ግቦች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
 
በደቡብ ክልል በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
 
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማጎልበት ይገባል ያሉት ተወካይዋ÷ያለእድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ እና መሰል የሴቶችን ህይወት የሚፈታተኑ ድርጊቶችን ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።
 
አቶ ርስቱ ይርዳ÷መንግስት የህብረተሰቡን የጤና ተደራሽነት ለማጎልበት የጤና ተቋማትን ማስፋፋት፣የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት እና ተዛማጅ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
 
ተቋማቱ በክልሉ ጌዴኦ ዞን በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት የመስክ ምልከታ በማድረግ ህብረተሰቡን ለመደገፍ እያደረጉት ያለውን ጥረት ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል።
 
እንደ ክልል ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ሌሎች ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች እንዳሉ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.