የተመድ የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በንግድ፣ በስራ ፈጠራ እና ኢንደስትሪ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላው የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና የልማት ኮንፈረንስ ጽሕፈጽ ቤት አስታወቀ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ ከተባበሩት መንግስታት የንግድ እና የልማት ኮንፈረንስ ጽሕፈጽ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፓውል አኪውሚ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ጽሕፈት ቤቱ በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ማለትም በአንጎላ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር በንግዱ እና ስራ ፈጠራው ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች ተነስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥም በንግድ፣ በስራ ፈጠራ እና ኢንደስትሪ ዘርፍ ለመስራት የተያዙ እቅዶችን በማብራራት በጽሕፈት ቤቱ የተካሄዱትን የፖሊሲ ጥናትም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ፓውል አኪውሚ ለሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ፍጹም በበኩላቸው÷ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ፖሊሲዎችን ከማናበብ እና ያሉትን ልዩነቶች ከመፍታት አንፃር በመንግስት በኩል እየተሰራ ያለውን ተግባር አስረድተዋል፡፡
ፖሊሲው በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ከምትሄድበት የልማት አቅጣጫ ጋር የተናበበ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ሃላፊዎቹ በቀጣይ በጋራ በመስራት በኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ላይ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።