የአማራ፣ ጋምቤላና ሲዳማ ርዕሳነ መስተዳድሮች ለጥምቀት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጅሉ እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በመልዕክታቸው ፥ “የጥምቀት በዓል የአንድነታችንና የአብሮነታችን መገለጫ ከመሆኑም በተጨማሪ የሀገርና የህዝብ ሃብት እንዲሁም የዓለም ቅርስ ነው” ብለዋል።
ልዩ ልዩ በዓላትን በማልማትና በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
“በዓሉን ስናከብርም ከቂምና ጥላቻ ርቀን ትብብርና አብሮነት የምንገነባበት፣ ለእውነት የምንጸናበትና ለአካባቢያችን ሰላም በአንድነት የምንቆምበት ሊሆን ይገባል” ብለዋል ርዕሰ መሰተዳድሩ።
የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጅሉ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው፥ በዓሉ ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሀገሪቱ መልካም ገፅታን ከመገንባትና የቱሪስት ፍሰትን ከማጎልበት አንፃር ጉልህ ሚና ያለው በዓል እንደሆነ ነው የገለጹት።
በዓሉ በክልሉ ሲከበርም ሰላምንና አብሮነት በሚያጠናክር እና መከባበርንና መተሳሰብን በሚያጎለብት እንዲሁም ሀገራዊ ገፅታን በሚያሳድግ መልኩ ማክብር እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመልካም ምኞት መግለጫቸው ፥ ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችንና አቅመደካሞችን በማገዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።
መተሳሰብ አብሮነትና ጠንካራ አንድነት ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የበዓሉን አስተዋጽኦ መጠቀም ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል ።