ላሚን ያማል ጋር የደረሰው 10 ቁጥር ማልያ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አብዛኞቹ ክለቦች ትልልቅ ታሪክ የተሰራባቸውን ማልያዎች እንዲሁ በቀላሉ የትኛውም ተጫዋች እንዲለብሰው አይፈቅዱም፡፡
ትልልቅ ተጫዋቾች ለብሰውት ታሪክ ሰርተው ያለፉበትን ማልያ በአጋጣሚ የመልበስ ዕድል አግኝተው ለብሰው የተጫወቱ አንዳንድ ተጫዋቾች የማልያው ክብር እና ዝና ሲከብዳቸው ይስተዋላል፡፡
በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ዘመን አይሽሬ ታሪክ ከተሰራባቸው የማልያ ቁጥሮች መካከል 10 ቁጥር ማልያ ቀዳሚው ነው፡፡
በካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ብዙ ታሪክ የተሰራበት እና ታላላቅ ተጫዋቾች የለበሱት 10 ቁጥር ማልያ አሁን ተስፈኛው ኮከብ ላሚን ያማል ጋር ደርሷል፡፡
ስፔናዊው ሉዊስ ሰዋሬዝ ሚራሞንቴስ በካታላኑ ክለብ ባርሴሎና 10 ቁጥር ማልያን ከፈረንጆቹ 1955 እስከ 1961 ለብሶ መጫወት ችሏል፡፡
ሉዊስ ሰዋሬዝ ሚራሞንቴስ የባሎንዶር ሽልማትን በፈረንጆቹ 1960 ያሸነፈ ሲሆን ሽልማቱን በማሸነፍም የመጀመሪያው ስፔናዊ ተጫዋች ነው፡፡
ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በባርሴሎና ቤት 10 ቁጥር ማልያ ለብሶ በመጫወት በዘመን ቅብብል ሁሌም የሚወሳበትን ታሪክ የሰራ ሌላኛው ኮከብ ነው፡፡
ጋሪ ሊንከር፣ ፔፕ ጋርዲዮላ፣ ሮማሪዮ፣ ጂኦቫኒ፣ ሪቫልዶ እና ሪኬልሜ በባርሴሎና ቤት ሌሎች 10 ቁጥር ማልያን ለብሰው የተጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
በተለይም በቅርብ ዓመታት ይህንን 10 ቁጥር ማልያን ለብሰው ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ሮናልዲኒሆ ጎቹ እና ሊዮኔል ሜሲ ምርጥ ብቃታቸውን ለዓለም እግር ኳስ ቤተሰብ አሳይተዋል፡፡
ሮናልዲኒሆ ጎቹ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ሳይጠገብ ከሜዳ ቢርቅም ይህንን ማልያ ለብሶ በድንቅ ጥበብ የእግር ኳስ ቤተሰቡን አዝናንቷል፡፡
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ሌላኛው 10 ቁጥር ማልያን ለብሶ በባርሴሎና ከዘመን ዘመን የሚነገር ታሪክ የሰራ ተጫዋች ነው፡፡
ሜሲ በባርሴሎና ቆይታው በዚህ ማልያ ተዘርዝረው የማያልቁ ዘመን አይሽሬ ታሪኮችን በወርቅ ቀለም ፅፎ አልፏል፡፡
ትልቁን የግል ሽልማት ባሎንዶርን ደጋግመው ማንሳት የቻሉ ተጫዋቾች የለበሱትን ይህን 10 ቁጥር ማልያ በቅርቡ የመልበስ ዕድል አግኝቶ የነበረው ስፔናዊው የፊት መስመር ተጫዋች አንሱ ፋቲ የተጠበቀውን ያህል ብቃቱን ማሳየት አልቻለም፡፡
አንሱፋቲ 10 ቁጥር ማልያን የተረከበው በክለቡ አይነኬ ታሪኮችን ሰርቶ ካለፈው ከሊዮኔል ሜሲ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ስፔናዊው የፊት መስመር ተጫዋች አንሱፋቲ በባርሴሎና ቤት ትልቅ ተስፋ ቢጣልበትም ከጉዳት እና ከአቋም መውረድ ጋር በተያያዘ የተጠበቀውን ያህል ሜዳ ላይ መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡
አንሱ ፋቲ በባርሴሎና በወጥነት መጫወት ባለመቻሉ ለብራይተን በውሰት ተሰጥቶ ቆይቶ በድጋሚ በውሰት ውል ወደ ሞናኮ አቅንቷል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በወጥነት ምርጥ ብቃቱን ያሳየው ወጣቱ ኮከብ ላሚን ያማል ተረኛው 10 ቁጥር ለባሽ ሆኗል፡፡
ላሚን ያማል ትልልቅ ከዋክብቶች እና የባሎንዶር አሸናፊዎች ለብሰውት የተጫወቱትን ማልያ ለብሶ በአዲሱ የወድድር ዘመን እንመለከተዋለን፡፡
ወጣቱ ኮከብ ምርጥነቱን በየጨወታው የሚያሳይ ሲሆን እስከ ባሎንዶር አሸናፊነት ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
ስፔናዊው ኮከብ ላሚን ያማል የእግር ኳስ ችሎታው ድንቅ ቢሆንም አንዳንድ የሚያሳያቸው ባህሪያት እያስተቸው ይገኛል፡፡
የ18 ዓመቱ ኮከብ አንዳንድ ተግባራት በእግር ኳስ ሕይወቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የብዙዎች ስጋት ቢሆንም በቀጣይ በ10 ቁጥር ማልያ የሚሰራቸው ታሪኮች ከወዲሁ ይጠበቃሉ፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ