መንግስት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዘላቂ ለማድረግ እየሰራ ነው-አቶ ታዬ ደንደአ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዘላቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ፡፡
ሴኪዩሪቲ ስተዲስ የተሰኘ ተቋም ከኦፕን ሶሳይቲ አፍሪካ ጋር በመተባበር “የግጭት ማቆም ስምምነትን ወደ ሁሉን አቀፍ ሐገራዊ ሰላም ማሸጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ በሁለቱም አካላት በኩል ሰላሙን ለማጽናት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።
ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውና ሰብዓዊ ድጋፍፎች መቅረባቸውም ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግም የተሃድሶ ኮሚሽን በማቋቋም በጦርነቱ የተሳተፉ ዜጎችን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ በቅርቡ በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የግጭት ማቆም ስምምነት ወደ ዘላቂ ሐገራዊ የሰላም ግንባታ ሂደት ለመቀየር የሚቻልበትን ዘርፈ ብዙ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦች በመለየት ለባለድርሻ አካላት ለማቅረብ ያለመ ነው ተብሏል።
በዘመን በየነ