የቻይናው ሲሚንቶ አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ በዘርፉ መዋዕለ ነዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከሲኖማ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሊቀመንበር እና የሲ ኤን ቢ ኤም ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሉ ያን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኩባንያው በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ተፈራ÷ ኩባንያው በኢትዮጵያ ባሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከዲዛይን ጀምሮ በግንባታ ረገድ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው የግንባታ ስፋት አንጻር የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንም አምባሳደር ተፈራ አስረድተዋል፡፡
ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ቢሰማራ የጋራ ተጠቃሚነቱ ሰፊ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 18 እስከ 20 ቀን 2015 በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኩባንያው እንዲሳተፍ መጋበዛቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሉ ያን በበኩላቸው÷ ለአንድ ሀገር ዕድገት ሲሚንቶ እና ብረት ወሳኝ ግብዓቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ዘመኑ ያፈራውን ምርጥ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖ የማይኖረው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመገንባት ሐሳቡ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የኩባንያው ኃላፊ በኤምባሲው የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው በኢንቨስትመንት ፎረሙ የሚሳተፍ ቡድን እንደሚልኩ አረጋግጠዋል፡፡