Fana: At a Speed of Life!

በጦር መሳሪያ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦር መሳሪያ በመታገዝ በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 4 ግለሰቦች ከ20 ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ፡፡
 
ተስፋዬ ጌታቸው፣ ተገኝ ሞቲ ፣ ባይሳ ተስፋዬ እና አዱኛ ኦልጅራ የተባሉት ተከሳሾች በቡድን ተደራጅተው በለሊቱ ክፍለ ጊዜ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ በጦር መሳሪያ የታገዘ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
 
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከግል ተበዳዮች መረጃው እንደደረሰው በአፋጣኝ የምርምራና የክትትል ቡድን በማቋቋም ባከናወነው የክትትል ስራ ግለሰቦቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም በአጥር ላይ በመዝለልና ቤት ሰብረው በመግባት በሽጉጥ አስፈራርተውና ደብድበው የተለያየ መጠን ያላቸውን ቴሌቪዥኖች፣ የጣት ቀለበትና የአንገት ሃብል፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ፣ ጥሬ ገንዘብና ሞባይል ስልኮችን ከተለያዩ ግለሰቦች ዘርፈው መውሰዳቸው ተጠቁሟል፡፡
 
ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ጊዜ በፈፀሙት በጦር መሳሪያ የታገዘ የዘረፋ ወንጀል መዝገብ ተደራጅቶባቸውና ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ጌታቸው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ ተገኝ ሞቲ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ባይሳ ተስፋዬ እና አዱኛ ኦልጅራ ደግሞ እያንዳንዳቸው በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
 
ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ማምለጥ የማይችል በመሆኑ በቀጣይም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ በቡድን ተደራጅተውና የጦር መሳሪያን በመጠቀም የውንብድና ወንጀሎችን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
ለዚህም ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ በፍርድ ቤትም ምስክር በመሆን የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.