Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለበዓላቱ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፊታችን ለሚከበሩ የትንሳኤ እና የዒድ አልፈጥር በዓላት ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ÷ መጪዎቹ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እያደረጉት ያለውን ቅድመ ዝግጅት በዛሬው ዕለት ገምግመዋል።

በመድረኩ በዓላቱ በድምቀት እንዲከብሩ የውሃና የመብራት አገልግሎቶችን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተጠቁሟል፡፡

የበዓል ዝግጅቱን በተመለከተ በመዲናዋ የሚገኙ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዕቅዳቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

በተለይ በበዓላት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የውሃና የመብራት አገልግሎት መቋረጦችን ለመቀነስ ስጋት ያለባቸውን ቦታዎች በመለየት የጥገና ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል፡፡

በበዓላቱ ቀናትም ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ መቋረጦች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የቴክኒክ ቡድን ተደራጅቷል ነው የተባለው።

ከእሳት አደጋ መከላከልና ዝግጁነት አንፃርም ከወዲሁ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን÷ በበዓላቱ ወቅት ለሚፈጠር ማንኛውም አደጋ ተቋሙ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ ተመላክቷል።

በዓላቱን የከተማዋ ነዋሪዎች በተረጋጋና፣ በሰላምና በደስታና በፍቅር እንዲያከብሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ አቶ ጥራቱ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በዚህም÷ በየተቋማቱ ቅርንጫፎችና በክፍለ ከተሞች ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙ በአስቸኳይ መፍታት እንዲቻል የኮማንድ ፖስት እንደተደራጀ መገለጹን የከተማዋ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.