ዶላር አሽሽተዋል በተባሉ የጉሙሩክ ኮሚሽን ሰራተኛና ነጋዴ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ዶላር አሽሽተዋል በተባሉ የጉሙሩክ ኮሚሽን ሰራተኛና ነጋዴ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበ፡፡
ክሱ የቀረበባቸው ተከሳሾች በጉምሩክ ኮሚሽን የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኛ የሆነው አዲስ አለም ድረስ እና ነጋዴ ነው በተባለው ህይወት መልኩ ታደሰ ላይ ነው።
በዚህም በቀረበ ክስ 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት የሰነድ ምርመራ ባለሙያ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት እና ለ2ኛ ተከሳሽ ለማስገኘትበማሰብና በመመሳጠር አላግባብ ዲክላራሲዮን እንዲሰራ የጉዞ መረጃ ሰነድ ሰጥቷል ሲል ዐቃቢህግ በክሱ አመላክቷል።
የብሔራዊ ባንክ የብር እና የውጭ ምንዛሬ አያያዝ ወሰን መመሪያ በመተላለፍ 2ኛ ተከሳሽ በዕለቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌለው እና ምንም አይነት የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ይዞ ባልገባበት ሁኔታ በተጭበረበረ መንገድ ይዞ እንደገባ በማስመሰል መመዝገቡን ዐቃቢህግ በክሱ ጠቅሷል።
በዚህ መልኩ ነጋዴ ነው የተባለው 1ኛ ተከሳሽ ሚያዚያ 15 ቀን 2010 ዓ/ም ከውጭ ሀገር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የውጭ ምንዛሬ ይዞ ባልገባበት ሁኔታ 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ሀገር ይዞ እንደመጣ በማስመሰል ዲክሌር አስደርጓል ሲል ዐቃቢህግ በክሱ ዘርዝሯል።
በዚህ መልኩ 2 ኛ ተከሳሽ በህገወጥ መንገድ ዲክሌር ካስደረገ በኋላ በንግድ ባንክ በከፈተው የዳያስፖራ ሂሳብ ገንዘቡን ገቢ በማድረግ ከ350 ሺህ ዶላር ውስጥ 166 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጭ ባንክ ያስተላለፈ እና የተጠቀመበት መሆኑን ዐቃቢህግ በክሱ ጠቅሷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 /ሀ እና አንቀፅ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 /ሀ እና 2 ላይ የተደነገገውን ተላልፈዋል ሲል 1ኛ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በልዩ ወንጀል ተካፋይነት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ከተከሳሾች መካከል 2 ኛ ተከሳሽ ብቻ ችሎት ቀርቦ ክሱ የደረሰው ሲሆን÷ ክሱ ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቅሶ 3 ገጽ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ዛሬ በዋለው ችሎት በጽሑፍ አቅርቧል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ዐቃቢህግ ምላሽ ካለው በአንድ ሳምንት መልሱን ከመዝገቡ ጋር እንዲያይዝ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ችሎት ያልቀረበውን 1ኛ ተከሳሽን ፖሊስ መጥሪያ በማድረስ የፊታችን ሚያዚያ 18 ቀን እንዲያቀርበው ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን÷ በዚሁ ቀጠሮ ቀን የ2 ኛ ተከሳሽ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያ ላይ መርምሮ ብይን እንደሚሰጥ ገልጿል።
በታሪክ አዱኛ