ሀገር አቀፍ የፀረ-አደንዛዥ ዕፆች የንቅናቄ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)”ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕፆች እና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እንታደግ” በሚል ቃል ሀገር አቀፍ የፀረ-አደንዛዥ ዕፆች የንቅናቄ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ እንዳሉት ÷ የሚታለመውን ዘላቂ ልማት ለማምጣት ለወጣቶች እና ታዳጊዎች በቂ ትኩረት መስጠት እና ስብዕናቸውን መቅረፅ ያስፈልጋል ብለዋል።
በከተሜነት መስፋፋት እና ሉላዊነት ምክንያት የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እየተስፋፋ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ÷ ይሁን እንጂ ወጣቶች በልኩ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ወጣቱ አደንዛዥ ዕፅ እና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመሞከር ለከፍተኛ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውሶች እየተዳረጉ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም በራሳቸው ባህል የሚኮሩ ሀገራቸውን የሚወዱ ወጣቶችን ለመፍጠር ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከመንግስት በተጨማሪ በርካታ የሲቪል ማህበራት በጉዳዩ ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ያነሱት ሚኒስትሯ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት ባለመገንባታቸው ወጣቶች በተለያዩ ሱሶች እየተዋጡ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የወጣቱን ስብዕና ለመገንባት ቀደም ሲል የተቋቋሙትን ማዕከላት በማጠናከር ወጣቶች መሰረታዊ የባህሪ እና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ የተጀመረው ንቅናቄ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይሰራል ብለዋል።
በምንይችል አዘዘው እና ሀይማኖት ወንዲራድ