በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክልል ማዕከላትና የዞን መዋቅር በጋራ በዳረጉት መድረክ ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ፡፡
ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ ከሚገኝ ገቢ በክልሉ የመደመር ትውልድ ቤተ መጽሐፍት ይገነባል ተብሏል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ÷ በክልሉ ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
መጽሐፍ ለሽያጭ ከማቅረብ ባሻገር በጥቅሙና ፋይዳው ላይ ተመስርቶ እንዲሸጥ፣ እንዲተዋወቅ እና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ እንዲሁም በየደረጃው ለሚገኘው ማሕበረሰብ የአስተሳሰብ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ስላለው ለሐሳብ መገንቢያ እንዲውል ይሠራልም ነው ያሉት፡፡
ለዚህ በጎ ዓላማ የክልሉ ሕዝብ በመጽሐፍ ግዥ እና በገቢ ማሰባሰቢያዎቹ በንቃት እንዲሳተፍ መጠየቃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ ለሶስት ወራት የሚቆይ የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር መጀመሩም ተጠቅሷል፡፡
በቀጣይም ባለሃብቶችና ሌሎች ደጋፊ አካላት በተገኙበት ተጨማሪ ገቢ የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል።