ከተማ አስተዳደሩ ከ256 ሺህ በላይ ለሆኑ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋሲካ እና የኢድ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ከ256 ሺህ በላይ ለሆኑ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ብቻ ለ3 ሺህ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርቷል፡፡
በተመሳሳይ በሁሉም ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር እየተካሄደ ነው።
ከማዕድ ማጋራት በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ 555 የታደሱ ቤቶችን ለነዋሪዎች አስተላልፏል፡፡
ይህን ተከትሎ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባለሀብቶችንና ነዋሪዎችን አስተባብረን ለነዋሪዎቾቻን ማዕድ ስናጋራ ያለንን ፍቅር እና አክብሮት እንዲሁም ቃል በገባነው መሠረት ዝቅ ብለን እያገለገልን መሆናችንን በተግባር የምናሳይበት ነው ብለዋል።
“መስጠት አያጎድልም” ያሉት ከንቲባዋ ካላቸው ቀንሰው ለወገኖቻችን ማዕድ እንድናጋራ ላገዙን ልበ-ቀና ባለሀብቶች፣ ነዋሪዎች እና በጎ ፍቃድ አገልጋዮች በከተማ አስተዳደሩ ስም ላመሰግናቸሁ እወዳለሁ ሲሉም አስፍረዋል፡፡
በፍቅርተ ከበደ