በ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሞጆ አዳማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የአዳማና የአካባቢውን ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት በ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሞጆ አዳማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 25 በመቶ የደረሰ ሲሆን በሥምንት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በአዳማ ከተማ ተጨማሪ የውኃ ፓምፖችን በመጠገን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ገልጿል፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አሕመድ አብዱጀሊል ለፋና ብሮድካስቲንግ እንደገለጹት÷ ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ጥገናውን በትኩረት በማከናወኑ በቀን ከ46 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃን በፈረቃ ማዳረስ ችሏል፡፡
የገቢ አሰባሰብን ለማዘመን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የቴሌ ብር ክፍያ ስርዓት መተግበሩንም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም በወር ከ10 ሚሊየን ብር በታች ያስገባ የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ አሁን ከ32 ሚለየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡
በጎህ ንጉሡ