በአዲስ አበባ ከ43 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ሕገ ወጥ መሬት ታግዷል- ኮሚቴው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፀረ ሙስና ኮሚቴ ከሕዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሕገ ወጥ የተገኘ 43 ሺህ 436 ነጥብ 44 ካሬ ሜትር መሬት ማገዱን አስታወቀ፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊድያ ግርማ እንደገለጹት÷ እገዳው በምርመራ ወቅት የተሰበሰቡትን ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ የተከናወነ ነው ፡፡
ከሕብረተሰቡ በነፃ ስልክ መስመር፣ በአካል እና በጥቆማ መቀበያ ሳጥኖች ከደረሱ 401 ጥቆማዎች መካከል 133 ለሕግ ምርመራ ቡድን ተመርቷል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም 130 የምርመራ መዝገቦች በማደራጀት እንደየ ወንጀሉ ባህሪ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና ወንጀል ፈፃሚዎችን በመለየት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
ከተደራጁ የምርመራ መዝገቦች መካከል 10 የምርመራ መዝገቦች ተጠናቀው ለፌደራል ዐቃቤ ሕግ መቅረባቸውን እና በ56 ግለሰቦች ላይ ክስ መቅረቡን አንስተዋል፡፡
የወንጀል አፈፃፀሙም የመንግስት ባዶ ቦታዎችን፣ ለከተማ ውበት ተብለው የተቀመጡ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመንግስት ሼዶችን ለግለሰቦች ይዞታ ማረጋገጫ መስጠት፣ ሀሰተኛ ካርታ በማዘጋጀት እና ሌሎችም የወንጀል ዘዴዎችን በመጠቀም የተፈፀመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የወንጀሉ ፈፃሚዎች ከመሬት ይዞታ ባለሙያ እስከ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች መሆናውም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ከተለያዩ ደላሎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር የሊዝ ዋጋ 29 ሚሊየን 249 ሺህ 955 ብር የሚገመት ጉዳት ማድረሳቸው በምርመራ መረጋገጡን ነው የኮሚቴው ሰብሳቢ የተናገሩት፡፡
በቅድስት ተስፋዬ