Fana: At a Speed of Life!

የስቅለት እና የፋሲካ በዓልን ስናከብር አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ሊሆን ይገባል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የስቅለት እና የፋሲካ በዓልን ስናከብር አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለስቅለት እና ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ ከራስ ይልቅ ለሌሎች መኖርን የሚያስተምር መሆኑን ገልጸው፤ አንዳችን ለአንዳችን ሰላም እና አብሮነት ልንከፍል የሚገባው ዋጋ ምን ያህል ትልቅ መሆኑን ያስተምራል ብለዋል።

ስለሆነም የስቅለት እና የፋሲካ በዓልን በምናከብርበት ወቅት ከጥላቻ በመራቅ እና በጎነትን እና ፍቅርን በመግለጽ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሕዝብ አገልጋዮች ከግል ጥቅምና ፍላጎት በመላቀቅ የመተጋገዝ እና የመተሳሰብ ዕሴት በማዳበር ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ያለንን ፍቅር በታማኝነት በማገልገል ልናረጋግጥ ይገባልም ነው ያሉት።

ያለንን አቅም አስተባብረን እጅ ለእጅ ተያይዘን የተጀመረውን የልማት ጎዳና ካስቀጠልን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ ማድረጋችን አይቀሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሚገጥሙ ችግሮችን መነጋገርን በማስቀደም መፍታት እንደሚገባ ገልጸው፣ ለፈተናዎች ሳንበገር የልማት እና የብልፅግና ትንሳዔያችንን እናፋጥን ብለዋል።

መላው የክርስት እና እምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ አቅመ ደካማ ወገኖችን በመርዳት፣ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን በመደገፍ እንዲሁም ማዕድ የመቋደስ ባህልን በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.