በአውሮፓ ግዙፉ የኑክሌር ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የፊንላንድ የኑክሌር ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሥራ ጀመረ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ፊንላንድ የተገነባው ይህ ማብላያ በአውሮፓ ትልቁ እንደሆነና በሠዓት 1 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተነግሯል፡፡
በግዙፍነቱም በዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ፊንላንድ ከሚያስፈልጋት ጠቅላላ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ 14 በመቶውን እንደሚሸፍንና ቢያንስ ለ60 ዓመታት ያኅል እንደሚያገለግል አር ቲ ዘግቧል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው ግንታው በፈረንጆቹ 2005 ላይ የተጀመረ ሲሆን÷ 2009 ላይ በሙከራ ደረጃ ኃይል ማመንጨት ጀምሮ ነበር፡፡
በዲዛየን ሥራው ላይ እንዲሁም ከሕግ አንጻር መቃኘት ያሉባቸው ጉዳዮች ፕሮጀክቱን አጓተውት ነው ከ14 ዓመታት በኋላ ሥራ ለመጀመር የበቃውም ተብሏል፡፡
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የፊንላንድ የኑክሌር ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች በፈረንጆቹ 1978 እና 1980 ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡
ፊንላንድ በፈረንጆቹ 2021 ከኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢዎቿ በድምሩ 14 ነጥብ 4 ቴራ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭታለች፡፡
ይህም ከሚያስፈልጋት አጠቃላይ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ አንድ ሥድስተኛውን ማለት ነው፡፡
የኑክሌር ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፊንላንድ ስዊድን እና ኖርዌይ ላይ የነበራትን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የግዢ ጥገኝነት እንድታቆም ይረዳታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡