Fana: At a Speed of Life!

የሸገርና አንበሳ አውቶብሶች በጥናት ላይ የተመሠረተ ስምሪት በማዘጋጀት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸገርና አንበሳ አውቶብሶች በጥናት ላይ የተመሠረተ አዲስ ስምሪት በማዘጋጀትቀልጣፋ የትራንፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

የሸገር እና አንበሳ አውቶብሶች የነበራቸውን ስያሜ እንደያዙ በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ የአውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በሚል ተቋም መዋሃዳቸው ይታወቃል።

አውቶብሶች የተዋሃዱበትን አላማ ለማሳካት በጥናት ላይ የተመሠረቱ አዳዲስ ስምሪቶችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሙኤል ፍስሃ ተናግረዋል።

ስምሪቱ በየአካባቢው ያለውን የትራንስፖርት ተጠቃሚ ብዛት እና የተመደቡ አውቶብሶችን ቁጥር መሠረት ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም አውቶብሶቹ በመዲናዋ ሁሉም አቅጣጫዎች ያለ ምንም መደራረብ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።

አሁን ላይም ሁለቱም አውቶብሶች 187 በሚበልጡ መስመሮች ላይ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በዚህም በቀን 900 የሚደርሱ አውቶብሶችን በማሰማራት ከ850 ሺህ በላይ ለሆኑ የመዲናዋ እና አካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ ተገዝተው የገቡት አውቶብሶችም የትራንስፖርት ችግር በሚስተዋልባቸው መስመሮች ላይ ተመድበው የማህበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡

ከውህደቱ በፊት ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች ተጠቃሚ በሌለባቸው መስመሮች ተደርበው ይመደቡ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ÷ አሁን ላይ መሰል ችግሮች መቀረፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮችን ለማስገወድም በሰራተኞች ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የአውቶብስ ተጠቃሚዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች ሲመለከቱም በነጻ የስልክ መስመር 8981 ላይ በመደውል ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.