Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በትንሳኤ በዓል ዋዜማና በበዓሉ ዕለት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ም/ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በበዓሉ ዋዜማ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 8 መገናኛ አካባቢ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ መንገድ ሲያቋርጥ የነበረ የ30 ዓመት ወጣት በተሽከርካሪ ተገጭቶ ህይወቱ አልፏል።

በበዓሉ ዕለት ደግሞ በአቃቂ ክፍለ ከተማከ ወረዳ 7 ሸገር ህንጻ አካባቢ በፒካፕ መኪና ላይ ከላይ ተጭኖ ሲጎዝ የነበረ ወጣት ፒካፑ ተገልብጦ ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ውሃ ልማት አካባቢ መንገድ ሲያቋርጥ የነበረ ሌላ አንድ ተጨማሪ ሰው በተሽከርካሪ ተገጭቶ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን ጠቅሷል።

በበዓሉ ዋዜማ በከተማዋ በ6 የተለያዩ ቦታዎች በ1ሺህ 242 አሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ የመጠጥ የትንፋሽ ፍተሻ ስራም 37 አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ አልኮል ጠጥተው መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በበዓሉ ዕለት በተለያዩ 5 አካባቢዎች አልኮል በጠጡ አሽከርካሪዎች ላይ በተሰራ የፍተሻ ስራ ከ956 አሽከርካሪዎች ውስጥ 14ቱ ብቻ ከመጠን ያለፈ አልኮል ጠጥተው መገኘታቸውን አንስተዋል።

በአጠቃላይ 51 ከመጠን ያለፈ አልኮል ወስደው ሲያሽከረክሩ በተገኙ ሹፌሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ነው የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል ባልደራስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የተናገሩት ምክትል ኮማንደሩ÷ በዚህ ጸብ ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 8 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.