ለሸዋል ዒድ በዓል ስኬት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሸዋል ዒድ በዓል አከባበር የተሳካ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ፡፡
አቶ ኦርዲን በድሪ የሸዋል ዒድ በዓል አከባበር ላይ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር መክረዋል፡፡
በውይይቱ ላይም የዘንድሮው የሸዋል ዒድ በዓል በልዩ ሁኔታ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዓሉ የሐረርን ባህል፣ ቅርስ፣ ታሪክና ዕሴት በሚገልፅ መልኩ እንደሚከናወንንም አመላክተዋል፡፡
ወንድማማችነትን በሚያጎለብት ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሚመራ የተለያየ ግብረ ሐይል መቋቋሙን ጠቅሰው÷ ግብረ ሐይሉ ከሚመለከታቸው አካላትና ተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ የበዓሉ አከባበር የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡