ለ125 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮ- ሩሲያ ግንኙነት በወዳጅነትና መተማመን ላይ የተመሠረተ ነው – አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ125 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮ-ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በወዳጅነት እና መተማመን ላይ የተመሠረተ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን፥ የኢትዮ-ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፈረንጆቹ 1898 ላይ መጀመሩን ይናገራሉ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው አምባሳደሩ፥ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን የመሠረቱት ከታሪካዊው የዓድዋ ድል ጥቂት ዓመታት በኋላ መሆኑ ደግሞ የሀገራቱን ወዳጅነት ልዩ እና ታሪካዊ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ ከዓድዋ ድል ወራት በኋላ በፈረንጆቹ 1896 ላይ የመጀመሪያው የሩሲያ የሕክምና ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሺህዎች ለሚቆጠሩ በጦርነቱ ለቆሰሉ ኢትዮጵያውያን ሕክምና ሠጥቷልም ብለዋል፡፡
ይህም ሁለቱ ሀገራት እንደ ጤና እና ትምሕርት በመሳሰሉት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይም በትብብር እንዲሠሩ መሠረት የጣለ መሆኑን አንስተዋል።
በፈረንጆቹ 1935 ላይም ኢትዮጵያ በፋሽስቱ ኃይል ስትወረር በሊግ ኦፍ ኔሽንስ መድረክ ወረራውን በፅኑ ያወገዘች የመጀመሪያዋ ሀገር ሩሲያ መሆኗን አክለዋል።
ሀገራቱ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው መልካም እና አስቸጋሪ ጊዜያትን ማለፋቸውን አስታውሰው፥ በተለይ በፈረንጆቹ 1959 ላይ አፄ ኃይለ ሥላሴ በሩሲያ ያደረጉት ጉብኝት ለሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር መሠረት የጣለ ክስተት ነበር ብለዋል።
ሩሲያ በፈረንጆቹ 1947ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ወዳጅነት የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታልን በአዲስ አበባ ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጧን አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን ገልፀዋል።
የሆስፒታሉ መገንባትም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ይበልጥ ያቀራረበ መሆኑን መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ሩሲያ በፈረንጆቹ 1966 ላይ የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩትን እና የመልካ ዋከና የውኃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን መሥራቷንም አውስተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 1989 ላይም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በርካታ የሙያ ትምህርትና ማሠልጠኛ ተቋማትን መሥርታ ከሀገሪቱ ህዝቦች ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደቻለችም ያስታውሳሉ።
ሩሲያ በሠጠችው ነፃ የትምህርት ዕድል ከ23 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሀገሪቱ መከታተላቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይም ሩሲያ በትምህርቱ ዘርፍ ትብብሯን ማሳደግ እንደምትፈልግ እና ለኢትዮጵያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል ለማመቻቸት በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ