ከንቲባ አዳነች ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በውይይቱ ÷ ባለሙያዎቹ ያሉባቸውን ጥያቄዎች እና ድጋፍ የሚሹባቸውን ጉዳዮች መጠቆማቸውን አስፍረዋል፡፡
በዚህም “አንዳንዶቹን ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር እንደምንፈታቸው ተግባብተናል” ነው ያሉት፡፡
ኪነ-ጥበብ ትውልድ የሚያንጽ አብሮ የመኖር ዕሴቶቻችንን የሚገነባ ነው ያሉት ከንቲባዋ በዚህም ከለውጡ ወዲህ በርካታ አንፊ ቴአትር ማሳያ ቦታዎች መገንባታቸውን ፤ የአዳዲስ ቴአትር ቤቶች ግንባታ መጀመራቸውን ፤ ነባሮቹን የማደስ እና አቅማቸውን የማጎልበት ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ቴአትር ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር ታሪካዊ ማንነታቸው ተጠብቆ በአሰራርና በአደረጃጀት ባለሙያው ነጻነቱ ተከብሮ በሙያው እንዲጠቀም ማድረግ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በመወሰን ለባለሙያው እና ለጥበብ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ በከተማዋ እየተገነቡ ካሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፊሎቹን የጎበኙ ሲሆን÷ በፈተና ውስጥም ቢሆን ህዝብን የሚጠቅሙ ስራዎች መሰራታቸውን አድንቀዋል ነው የተባለው፡፡