የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ በሰላም ረገድ አርዓያነትን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ መሆኑን ናሌዲ ፓንዶር ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሀገር ብቻ ሳትሆን በሰላም ረገድም አርዓያነትን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ተናገሩ።
“ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ሐሳብ በመንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ቁልፍ ሚና ለተወጡ አካላት የዕውቅና እና የምስጋና መርሐግብር በአዲስ አበባ ተካሒዷል፡፡
በሥነ ስርዓቱ ላይ ናሌዲ ፓንዶር ባደረጉት ንግግር÷ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የተፈታበት መንገድ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍትሄ መቅረፍ እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካዊያን የሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት የመንግስትና የሕወሃት አመራሮች ወደ ሰላም ለመምጣት ቁርጠኛ አቋም ማሳየታቸውን አስታውሰው÷ አፍሪካ ሕብረትን እና ሂደቱ እንዲሳካ ሚና የተወጡ አካላትን አመስግነዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዕውን መሆን የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ለተያዘው ግብ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂ ትግበራ ሁሉም ጥረት ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡
የሰላም ስምምነቱ ስኬት ወረቀት ላይ መፈረሙ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ ያለው ትግበራ መሆኑን ጠቁመው÷ የድሕረ ሰላም ስምምነት ትግበራው ባደረጉት ክትትል በትግራይ ክልል የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ትግበራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለመከላከያ ሰራዊትና ለሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ለማምጣት የተገባ ቃል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ወገኖች በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
መሰል የሰላም ሂደቶች አፍሪካ በ2063 አጀንዳ የበለጸገች፣ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አካታች እና ዘላቂ ልማት የተረጋገጠባት አህጉር የማድረግ ግብ እንዲሳካ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብቻ ሳትሆን ችግሮችን በሰላም በመፍታት ለአፍሪካ አርዓያነቷን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተቀረው የአፍሪካ ክፍል የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አህጉር መፍጠር፣ ሰብዓዊ መብት መከበር፣ የዜጎችን ነጻነት እና ብልጽግና ዕውን ማድረግ እንዲቻል በጋራ መስራት እንደሚገባም ጥሪ ቅርበዋል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!