አቶ ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ ሀገራት የሚየደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ ሀገራት የሚየደርጉትን ጉብኝት ዛሬ በታንዛኒያ ጀመሩ።
አቶ ደመቀ ዛንዚባር ሲገቡ የታንዛኒያ አቻቸው ሲቴጎሚና ታክስ ተቀብለዋቸዋል።
ጉብኝታቸውን በታንዛኒያ የጀመሩት አቶ ደመቀ መኮንን በቀጣይም÷ በኮሞሮስ፣ ቡሩንዲ እና ዩጋንዳ እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡
አቶ ደመቀ ከታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ጋር በሁለትዮሽና አከባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ላላት ግንኙነት ትኩረት እንደምትሰጥ አስረድተዋል፡፡
ግንኙነታቸው በኢኮኖሚው መስክም እንዲጠናከር ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በመተግበር ሰላምን ማፅናት እንደሚፈልግም ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት እልባት እንዲያገኝ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አያይዘውም የዓረብ ሊግ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንዳልሆነም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
በሱዳን ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡
ሳሚያ ሱሉሁ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም በአቪዬሽን፣ ቱሪዝም እና በባህል መስክ እንዲጠናከር ፍላጎቷ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታንዛኒያ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈንና ለማፅናት የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍም ነው ያረጋገጡት፡፡
የሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ከመግባባት ላይ መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ታንዛኒያ ውስጥ በአዘዋዋሪዎች ተታልለው በቁጥጥር ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተገቢው አያያዝ እንዲደረግለቸው አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።
በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፉት ወራት 2 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለሱ እና ቀሪዎቹንም ለመመለስ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!