የሐረሪ ክልል መንግሥት በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ሃዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ሃዘን ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግሥት ባወጣው የሀዘን መግለጫ ፥ የፖለቲካ አመለካከትን በዕውቀትና በእውነት ማራመድ የተሳናቸው የሀሳብ ድሆች ማሰብ የሚችሉ ባለ ብሩህ ራዕይ ሰዎችን ማጥቃት ብቸኛ አማራጫቸው ነው ብሏል።
በዚህ ዘመን ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል በሆነበት ክፍለ ዘመን፣ በሐሳብ የተለየንን ሁሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሣት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ማሳያ ነው ብሏል በመግለጫው።
የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ መፅናናትን እንደሚመኝ ከክልሉ መንገስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።