ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከፍተኛ ልዑክ በሽግግር ፍትሕ አተገባበር ሒደት ላይ ገለጻ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የፍትሕ ሚኒስቴር ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊዎች በሽግግር ፍትሕ ይዘትና አተገባበር ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ÷ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያስቻለ ነው ብለዋል።
መንግስት ከታጠቁ ሃይሎች ጋር ድርድር በማድረግ ሀገሪቱን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም አንስተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረቱ የተጀመረውን የሰላም ግንባታ እንዲደግፍም አምባሳደር ምስጋኑ ጠይቀዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ በበኩላቸው÷መንግስት በጦርነቱ ወንጀል የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግበትን የሽግግር ስርዓት የተለያዩ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰነዱም ተገቢውን ህጋዊ ሂደት አልፎ ከቀጣይ መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የገለጹት፡፡
በመድረኩ የሽግግር ሂደቱ አጠቃላይ ይዘት፣ መሰረታዊ መርሆችና አተገባበር ላይ ገለጻ ተደርጎ አባላቱ ላነሱት ጥያቄና እና አስተያየት ምላሽ መሰጠቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡