ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እየፈጠሩ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ እንዳሉት ፥ በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 16 ቀን 2015 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክ ብቻ እንዲፈጸም እየተደረገ ነው።
በዚህም ÷ በመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ ከአሽከርካሪዎች በኩል አካውንት ያለመክfት ችግር ይስተዋል እንደነበር ጠቁመwale::
አሁን ላይ ግን በቴሌ ብር ኤጀንቶች አማካኝነት ቀደም ብለው አካውንት እንዲከፍቱ እየተደረገና የተሻለ አገልግሎት በነዳጅ ማደያዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች የነዳጅ እጥረት እንዳለና ነዳጅ እያላቸው እንዳለቀባቸው በማስመሰል እንዲሁም በሙሉ አቅማቸው ባለመስራት ደንበኞች እንዲጉላሉና ሰው ሰራሽ ችግር እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ÷ ባለፉት ቀናት ያልተገባ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ ማደያዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የቃል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደነበር አስታወሰው ፥ በቃል ማስጠንቀቂያ የማይመለሱት ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም ጀርመን አደባባይ አካባቢ የሚገኝ ቶታል ማደያ ነዳጅ እያለው እንደሌለው በማስመሰል ዘግቶ በመቀመጡ እርምጃ እንደተወሰደበትም ነው የተናገሩት።
በዚህም ነዳጅ ማደያው ላልተወሰነ ጊዜ ነዳጅ እንዳይራገፍለት የሚያደርግ ውሳኔ መተላለፉን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ÷ በተለምዶ ሀያት ሰባ ሁለት የሚባል አካባቢ የሚገኝ ዳሎል የነዳጅ ማደያ በጥሬ ብር ነዳጅ ሲሸጥ በመገኘቱ እንዲታሸግ መደረጉን አክለዋል።
እርምጃው የተወሰደው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በኩል መሆኑን በመጠቆም ፥ በቀጣይም ህግና ስርዓትን በማያከብሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
ሌሎች የነዳጅ ማደያዎች የተጀመረውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት በአግባቡ እንዲተገብሩና በሙሉ አቅማቸውና በቅንነት እንዲሰሩም ነው ዳይሬክተሯ ያሳሰቡት፡፡
ይህ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ሕገ-ወጥ ግብይትን ለመከላከልና ነዳጅ እያላቸው የለንም በሚል መጉላላት የሚፈጥሩ ማደያዎችን በቀላሉ ለመቆጣጣር የሚያግዝ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡