ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት – ኢሪና ኤስ ኒዮኒ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢሪና ኤስ ኒዮኒ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ለአውሮፓ ህብረት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ብለዋል፡፡
በስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢሪና ኤስ ኒዮኒ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም ፥ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ህብረት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን ጠቅሰው ፤ ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላም በምታደርገው ጉዞ ላይ የህብረቱ ድጋፍ እንደማይለያት ገልጸዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት በዘላቂነት እንዲተገበር የአውሮፓ ህብረት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥም ነው ያብራሩት።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መደበኛና ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክርም አክለዋል፡፡
የሽግግር ፍትህ ስርዓት አተገባበርን አስመልክቶ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት ፥ በተለይ ተጠያቂነትና የሽግግር ፍትህ ለአፈፃፀሙ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ዘላቂ ሰላምን ለማግኘት ወሳኝ በመሆኑ የአውሮፓ ህብረት ሂደቱን በቅርበት እየተከታተለ ነው።
የሽግግር ፍትህ ስርዓቱን የማስፈጸም ሂደት ሁሉንም በሀገሪቱ ጉዳይ የሚመለከታቸውን አካላት በማካተት ዘላቂ ሰላምን ለማስጠበቅ ሁሉንም ያሳተፈ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት በቀጠናው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ፥ ሁለቱም ወገኖች ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጋልም ነው ያሉት።
በዚህም የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ግንኙነት በአጀንዳነት ግንባር ቀደም እንደሆነ ተገልጿል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ከፍተኛ የስራ ጉብኝት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም ፡- በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ ግንኙነት፣ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በአውሮፓ ህብረትና በአፍሪካ ህብረት አጋርነት ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።