“አቶ ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቁ መሪ ነበሩ”- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቁ መሪ ነበሩ ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች በአቶ ግርማ የሽጥላ አስከሬን ሽኝት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷የአቶ ግርማ ሞት ለእኛ አሳዛኝም፣ አስደንጋጭም ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ግርማ የማይሞት ዓላማ ያነገቡ መሪ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ላመኑበት እውነት ሕይዎትን አሳልፎ እስከመስጠትም ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ሞት ሥጋን እንጂ ዓላማን አይገድልም ያሉት ከንቲባዋ÷ አቶ ግርማ ማስመሰል አይችሉም፣ ለእውነት ኖረዋል ስለእውነትም አልፈዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቁ መሪ እንደነበሩ ገልጸው÷ የሕዝቦች ወንድማማችነት እና የኢትዮጵያ አንድነት የሚያስጨንቃቸው መሪ ነበሩም ብለዋል፡፡
አቶ ግርማ ዘመናቸውን ሁሉ ቤተሰባቸውን ትተው ሕዝብን ለማገልገል እንደሰሩም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ አሁን ባሉት የግርማ የትግል ወንድሞች ትከሻ ላይ ያረፈ ነውም ብለዋል ከንቲባዋ፡፡