አቶ ግርማ የተሰዋለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ከምንጊዜውም በላይ በመረባረብ ብልፅግናችን በፅንፈኞች የማይደናቀፍ መሆኑን እናረጋግጣለን-አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ግርማ የተሰዋለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ከምንጊዜውም በላይ በመረባረብ ብልፅግናችን በፅንፈኞች የማይደናቀፍ መሆኑን እናረጋግጣለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
አቶ አደም በአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን ሽኝት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷አቶ ግርማ ሃገራዊ ራዕይን የሰነቁ፣በሳል እና ቁርጠኛ የህዝብ አገልጋይ የነበሩ የህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ልዩነት ሰባኪነትን የሚፀየፉ፣ ጽንፈኝነትን አምርረው የሚታገሉ እና ሁልጊዜም ለፍትህ እና ለእኩልነት የቆሙ እውነተኛ የብልፅግና አመራር እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡
በምክንያታዊነት የሚሞግቱ፣ ጀግናና ልባም መሪ መሆናቸውንም አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል፡፡
አቶ ግርማ ለሀገር ፣ለህዝባችን እና ለፓርቲያችን ያበረከቱትን አስተዋፅዖ አንረሳውም ያሉት አቶ አደም÷ መላው የፓርቲው አመራር እና አባላት አቶ ግርማ የተሰዋለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ከምንጊዜም በላይ በመረባረብ ብልፅግናችን በፅንፈኞች የማይደናቀፍ መሆኑን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
የህዝብ መሪን እየገደሉ፤ የንፁኃንን ዜጎች በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነትን መብት እየገፈፉ ሊሳካ የሚችል ዘላቂ ጥቅም የለም ነው ያሉት፡፡
“ወንድሞቻችን የገደሉ ፅንፈኞችን ለሕግ ለማቅረብም አበክረን እንሳራለንም” ብለዋል፡፡
ህዝቡ የዜጎችን ክብር ያለው ባህልና ታሪክ መሰል ለማጉደፍ እንደዚህ አይነት ነውረኛ ድርጊት የሚፈፅሙ ፅንፈኞችን ስርዓት ለማስያዝ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡