ፔንታገን ለዩክሬን የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር እርዳታ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የሚውል 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የገንዘብ እርዳታው በዋናነት የዩክሬንን መከላከያ የማጠናከር አላማ ሲኖረው፥ በተለይም ለአየር መቃወሚያ፣ ለጦር መሳሪዎች እና ለሚደረጉ የጦር መሳሪያ ግዥ ሥምምነት ማስፈጸሚያ ይውላል ነው የተባለው።
እንደ ፔንታገን ገለፃ÷ የተደረገው ገንዘቡ ዩክሬን በአስቸኳይ የምትፈልጋቸውን የጦር መሳሪያዎች ለማሟላት እና ወታደራዊ ሀይሏን ለማጠናክር የሚያግዝ ነው፡፡
እርዳታው አሜሪካ በቀጥታ የምትሰጠው ሳይሆን ለኬቭ በምታደርገው የዩክሬን የደህንነት ድጋፍ ማዕቀፍ በኩል ድጋፍ የሚፈጸም ይሆናል ነው የተባለው።
በዚህም መሳሪያዎቹ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች እና ከአጋርና ወዳጅ ሀገራት ኩባንያዎች ተገዝተው በተዘዋዋሪ ለዩክሬን ይቀርባሉ መባሉን ምንጮች ዋቢ ያደረገው የአር ቲ ዘገባ ያመላክታል።
አሜሪካ እስካሁን በተለያየ መልኩ ለዩክሬን ከ37 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓን መረጃዎችን የጠቀሰው ዘገባው ያመላክታል።
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካ እና አጋሮቿ በዩክሬን ጦርነት በቀጥታ ባይሳተፉም እስከ ፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ 100 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን ድጋፍ ማድረጋቸውን ትገልፃለች፡፡
አሁን ላይ የአሜሪካ የእዳ ጣሪያ ከልክ አልፏል በሚል የባይደን አስተዳደር ከሪፐብሊካኖች ጋር ቢፋጠጥም ዋሺንግተን ግን ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አሁንም ቀጥላለች።