የአረብ ሊግ ሀገራት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም- ጋዜጠኛና ተንታኝ ኩንጉ አል ማሃዲ አዳም
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የአረብ ሊግ ሀገራት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም ሲል ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛና ተንታኝ ኩንጉ አል ማሃዲ አዳም አስተያየቱን ሰጠ፡፡
ጋዜጠኛ አል ማሃዲ የአረብ ሊግ ሀገራት የግብፅ ቃል አቀባይ ሆነው መንቀሳቀሳቸው ተገቢ አይይደለም ሲልም ነው የገለጸው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሳዑዲ አረቢያ ወይም ሶሪያ አልያም የትኛውም አረብ ሀገር እራሳቸውን ማልማት በሚገባቸው ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እንደማያውቅ የገለፀው ጋዜጠኛው፥ አፍሪካም የራሷን ችግር ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንድትፈታ መተው ይገባል ብሏል፡፡
የአረብ ሊግ ዓርብ ዕለት በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ባካሄደው ስብሰባ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ያቀረበው ዕቅድና የመፍትሄ ሀሳብ፥ የአፍሪካ ማህበራዊ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ገሃነም የመውረድ ያክል ፍርሃት እንደሚለቅባቸው ማሳያ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እና ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት በመንግስት፣ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ባሉ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባ መሆኑንም አስታውሷል፡፡
ግድቡ በኤሌክትሪክ እጦት ለሚቸገሩ 65 ሚሊየን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አግልገሎት የሚያቀርብ እንዲሁም ሥራ አጥነትን በመቅረፍ የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ችግር ወደ አንድ ደረጃ ያሻግራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት የግንባታ ሂደቱ አሁን ላይ 90 በመቶ መድረሱንም አስታውሷል፡፡
ይሁንና ግብፅ የ1959 ኢትዮጵያን ያላካተተ ስምምነት ተንተርሳ የውሀ ድርሻየን ይቀንስብኛል በማለት ሆን ብላ በፕሮጀክቱ ተቃራኒ መቆሟንም ነው የጠቆመው፡፡
ካይሮ የህዳሴው ግድብ ያለግብፅ ፈቃድ ነው የተገነባው የምትል ሲሆን ይህም ለሀገሪቱ ደህንነት ስጋት ደቅኗል በማለት እንደምትከራከር ነው ባሰፈረው ፅሁፍ ያነሳው።
የአፍሪካ ህብረት የግድቡን የውሀ ሙሌት እና አጠቃላይ ክንዋኔ በተመለከተ የሦስትዮሽ ስምምነት ላይ ለመድረስ እያደራደረ እንደሚገኝ አል ማሃዲ ገልጿል፡፡
ነገር ግን ግብፅ ጉዳዩን የደህንነት ስጋት እንደሆነ አድርጋ ለአረብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በማቅረብ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ባደረገችው ሂደት÷ ስብሰባው በማጠቃለያው በአንድ ወገን የሚደረገው የግድቡ የውሀ ሙሌት እንዲቆም ለኢትዮጵያ እና ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ትዕዛዝ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት ያደረገው አካሄድ ተቀባይነት የለውም ሲል አፅንዖት በመስጠት ተናግሯል፡፡
በዚህም ግብፅ የአረብ ሊግ እና የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ህብረት በሚደረገው ድርድር መሀል ጣልቃ እንዲገቡ በመጋበዝ የምታደርገው ሩጫ የአፍሪካ ህብረትን የማደራደር እና መፍትሄ የማምጣት አቅም አኮስሳ እንደምትመለከት ማሳያ ነው ሲልም ገልጿል፡፡
የአረብ ሊግ አባል ያልሆነችውን ነገር ግን የጉዳዩ ዋና ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያን በጄዳ ስብሰባ ተቀምጦ እንዴት ትዕዛዝና አቅጣጫ መስጠት ይቻላል ሲልም በአግራሞት ግብፅን ሸንቆጥ አድርጓታል፡፡