የሰብዓዊ እርዳታ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው – የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰብዓዊ እርዳታ ለታለመለት ዓላም ይውል ዘንድ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭት ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማሰራጨት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስቷል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታትድርጅት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የሰብዓዊ እርዳታን ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚያውሉ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ከክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡
የሚሰራጩ የሰብዓዊ እርዳታዎች በትክክል ለተጎጂዎች እንዲደርሱም በተዘረጋው ስርዓት መሰረት አስፈላጊውን ቁጥጥር የማድረግ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል፡፡