አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን ቻይና በኢትዮጵያ የምታደርገውን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደምታጠናክር ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የመሰረተ ልማት ግንባታ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን አረጋገጡ፡፡
የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ኢንሼቲቭ የ10 ዓመት ትግበራን በተመለከተ የምክክር መድረክ ተካሄዷል::
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ÷ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ እና የተለያዩ ግንባታዎች በ10 ዓመቱ የቻይና የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡
በተለይ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ተገንብቶ ወደ ተግባር ከተገባ በኃላ የሀገሪቱን ከፍተኛ የገቢና ወጪ ዕቃዎች በማሳለጥ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን በበኩላቸው÷ የቻይና መንግስት ተግባራዊ እያደረገ ባለው የመንገድ ግንባታ ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ በተሻለ መልኩት ተጠቃሚ እየሆነች ነው ማለታቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይም ቻይና ይህን ኢንሼቲቭ በተጠናከረ መልኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለማከናነወን እንደምትሠራ አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል በአምባሳደር ዣኦ ዢዩአን የተመራ ልዑክ ከፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ጋር ባደረገው ውይይት÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሕግ ትብብር በሚጠናከርበት ዙርያ መክረዋል፡፡
ተጨማሪም የዐቅም ግንባታ ድጋፎች በሚደረጉበት እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የቻይና መንግስት ትብብርና ድጋፍ በሕጉም ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ዓለምአንተ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን በበኩላቸው÷ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በሕግና ፍትሕ ዙርያ የምታደርገው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡
በወንጀል በመጠርጠራቸው ምክንያት በኢትዮጵያ በእስር የሚገኙ የቻይና ዜጎች ጉዳይ በሕግ አግባብ በተቻለ ፍጥነት መፍትሔ እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡