Fana: At a Speed of Life!

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከ ጂ አይ ዜድ ጋር በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) የንግድ ሥራን አመቺ ለማድረግ እና በዘርፉ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሠነድ ተፈራርመዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የጥራት መሠረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን÷ የንግድ ሥራ ምቹና ውጤታማ እንዲሆን የንግድ ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የተለያዩ ሪፎርሞችን በማካሄድ መመሪያዎችን የማሻሻልና አላስፈላጊ መስፈርቶችን የማስቀረት ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡

የመግባቢያ ሠነዱ መፈረምም÷ቀደም ብለው እየተሠሩ የነበሩ የንግድ ሥራ አመቺነት ሥራዎችን ለማጠናከር እንዲሁም ምቹ፣ ቀልጣፋና ዲጂታል የንግድ አገልግሎትን ለማጠናከር ያግዛል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጂ አይ ዜድ ቤይክ ኘሮጀክት ከሚኒስቴሩ ጋር ለሚተገበረው ኘሮጀክት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።

በጂ አይ ዜድ ቤይክ ኘሮጀክት በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ኤሊ ሳዋያ ስምምነቱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ስርዓትን÷ ከግብር ከፋይ ምዝገባ፣ ከብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጪ ቢሮ እና ከሠነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር በማጣመር በአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርጋል ብለዋል።

የኘሮጀክቱ ዓላማ ከንግድ ምዝገባና ፈቃድ ጋር በተያያዘ የሚመጡ የጊዜ እንዲሁም የገንዘብ ብክነትን ለመቀነስ እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ስራ የመጀመር ሂደትን ለማቅለል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ 965 የተሰኘ የጥሪ ማዕከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ ተደርጓል፡፡

የጂ አይ ዜድ ቤይክ ኘሮጀክት ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ ምቹነትን ለማቅለል በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኝ ኘሮጀክት ነው፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.