Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና በሸገር  ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል በተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ተፈቀደ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን የሽብር ጥርጣሬ መነሻ ምክንያቶችን እና በተጠርጣሪ የተነሱ መከራከሪያ ነጥቦችን መርምሮ ነው ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ የፈቀደው።

ተጠርጣሪዎቹ  ያድንናኦል ሱራፌል፣ ሚካኤል ዮሐንስ  እና ወሳቡ ደረጀ  ይባላሉ።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ  ግለሰቦቹ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩበትን መነሻ ምክንያት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ  የሸኔ የሽብር ቡድን አባል በመሆን፣ ከቡድኑ አመራሮች ጋር በአካልና በስልክ  በመገናኘት፣ ወጣቶችን በመመልመል፣ በመገናኛ ዘዴዎች መረጃዎችን በማቀበል ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት አብራርቷል።

በተጨማሪም ከሽብር ቡድኑ አመራሮች ተልኮ በመቀበል፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በማቀድ 2 ሺህ 63  ጥይቶችን  በተሽከርካሪ በመያዝ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል  ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ  ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ መሆኑን ጠቅሶ÷ የምርመራ ስራውን በማስረጃዎች አካቶ ለመቅረብ እንዲያስችለው የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ምንም ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር  የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ማጣሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ተፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.