Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞችን ማስተናገዷ ምስጋና የሚያሰጣት ነው – ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሊመንትስ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምስጋና የሚያሰጣት ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሊመንትስ ተናገሩ።

በምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሊመንትስ የተመራ ልዑክ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን የጀዌ ስደተኞች ጣቢያን ጎብኝቷል።

ኬሊ ክሊመንትስ እና ልዑካቸው በካምፑ ለስደተኞች የተሰሩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችንና የመሰረተ ልማት ተቋማትን ተመልክተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሯ በወቅቱ እንደገለጹት÷ በዓለም ላይ ያለው የስደተኞች ቁጥር መብዛት የምግብ እጥረት እንዳያስከትል ስደተኞች በልማት ተሳታፊ መሆን መቻል አለባቸው፡፡

ለጋሽ ድርጅቶች ከሚያደርጉት እገዛ በተጨማሪ ስደተኞች በሚኖሩበት ካምፕ ስራ ፈጣሪና ገቢ አመንጪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው÷የጉብኝቱ አላማ ለጋሽ ድርጅቶች ስደተኞች በሚኖሩባቸው ካምፖች ያሉ ችግሮችን የማሳየትና በቀጣይ ከተባባሪ አካላት ጋር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ክልል 383 ሺህ ስደተኞች በሰባት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አገልግሎት እያገኙ እንደሚገኙም መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.