በሳንባ በሽታ መከላከል የተሻለ ለውጥ ላስመዘገቡ የአፍሪካ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት እና አጋሮች በሳንባ በሽታ መከላከል የተሻለ ለውጥ ላመጡ የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀረበች።
የሳንባ በሽታን አስመልክቶ የተዘጋጀው የአፍሪካ ቀጣናዊ ስብስባ በታንዛንያ አሩሻ ተካሄዷል።
በጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራ የልዑካን ቡድን በስብስባው ላይ ተሳትፏል።
ስብሰባውን ያዘጋጀው ኤች አይ ቪ ኤድስን፣ የሳንባ በሽታን እና ወባን ለመከላከል የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ፈንድ ነው።
በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2030 የሳንባ በሽታን ለማጥፋት የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ÷ ኢትዮጵያ የሳንባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ባከናወነችው ስራ ለውጥ አምጥታለች ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የሳንባ በሽታን በመከላከል ያገኘቻቸው መልካም ለውጦች በፋይናንስ ድጋፍ ቅነሳ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ገጥሞታል፤ ይህም በሳንባ በሽታ የተቀመጡ ግቦች ላይ መድረስን አስቸጋሪ አድርጎታል” ተብሏል።
ኢትዮጵያ በአሩሻ አዋጅ አማካኝነት በፈረንጆቹ 2030 የሳንባ በሽታን ለማጥፋት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ መገለጹን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡