Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል መሬትን ከታለመለት አላማ ውጭ ባዋሉ 129 ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል መሬትን ከታለመለት አላማ ውጭ ባዋሉ 129 ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ 464 ሚሊየን ብር የካፒታል በጀት ተመድቦ በጎንደር፣ በእንጅባራ፣ በወረታ፣ በከሚሴ፣ በሃርቡ እና በደባርቅ ያሉ የመንገድ፣ የመለስተኛ ድልድይና የመብራት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይኸነው አለም እንደገለጹት÷ከፌደራልና ክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ደረጃቸውን የጠበቁ 5 ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቡሬ፣ በደብረብርሃን፣ በኮምቦልቻ፣ በባህርዳርና አረርቲ (የግል) ፓርኮች ተገንብተው ለባለሃብቶች ቀርበዋል፡፡

ባለፉት ወራት 32 ሺህ 278 ሄክታር መሬት ለባለሃብቶች ማስተላለፍ እንደተቻለ ጠቅሰው÷ከ1 ሺህ 328 በላይ በአምራችና ከ30 ሺህ 950 ሄክታር በላይ በግብርና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከ3ኛ ወገን ነጻ በማድረግ ማስተላለፍ ተችሏል ብለዋል፡፡

ቢሮው የተቋቋመበት ዓላማ እርምጃ መውሰድ ሳይሆን ባለሃብቱን ደግፎ ወደ ስራ ማስገባት ነው ያሉት አቶ ይኸነው አለም÷ ነገር ግን ያልተገባ ጥቅም ፈልጎ በመጣ ባለሀብት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረት በበጀት አመቱ እስካሁን 129 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ 592 ነጥብ 29 ሄክታር መሬት ወደ መንግስት የመሬት ባንክ ማስመለስ እንደተቻለ ሀላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው ባለሃብቶች መካከል 84 ነጥብ 32 በመቶ በአምራች ዘርፍ ሲሆን፥ ቀሪው ደግሞ በሌሎች ዘርፎች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ52 በመቶ ወደ 60 በመቶ እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.