Fana: At a Speed of Life!

በዮርዳኖስ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብት የሚያስጠብቅ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዮርዳኖስ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የስራ እና ክሕሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ÷ ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በዮርዳኖስ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን  መብትና ጥቅም የሚያስጠብቁ  ጉዳዮች ላይ ምክክር በማካሄድ ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡

33 ሺህ ኢትዮያውያን በሚገኙባት ዮርዳኖስ የዓለም አቀፉን የስራ ድርጅት የሰራተኛና አሰሪ ግንኙነት መስፈርቶች ጨምሮ የደመወዝ ጭማሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ፣ ሕክምና እና ኢንሹራንስን በሚመለከት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የስራ ሰዓትና እረፍትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሁለቱ ሀገራት ተደራዳሪ ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ላይ ከዮርዳኖስ የንግድ፣  ኢንዱስትሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር  ዮሴፍ ሻማሊ ጋር ሰፊ ምክክር አድርገን ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ ቀደም ሲል ይላኩ የነበረውን የቤት ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል መላክን ለማካተት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የሚገኙ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንንም የሚያካትት ሲሆን ÷ በየዓመቱ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግንም ከግዴታ ያስገባ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በየጊዜው የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ተመስርቶ ክትትል የሚደረግበትና የሚታደስ ይሆናል ሲሉም ነው ሚኒስትሯ ያነሱት፡፡

ስምምነቱ ከስራ ስምሪት ግንኙነት ባሻገር ኢትዮጵያ  ከዮርዳኖስ መንግስትና ህዝብ ጋር ያላትን የቆየ በእህትማማችነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ፣  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ትብብር የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.